ቆንጨራ ያላነሳ ሃይማኖት አልነበረም!

0
44

ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ, PH.D.*

ክፍል 1


አብዛኛውን ጊዜ የኅይማኖት ምንጮች ሁሉ በጥልቀት አንብበው ‹የተረዱ› ሰዎች (1) ለብዝሃ ኅይማኖት እውቅና ይሰጣሉ (2) ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላማዊ ግንኙነት እንድፈጥሩና በሰላም አብሮ እንድኖሩ ያበረታተሉ (3) ጽንፈኝነትን ይከላከላሉ ወዘተ። ጀርመናዊው ምሁር ማክስ ሚለር ትክክል ነበር ማለት ነው! ሚለር ‹‹በእኛ አይን የጐረቤታችን ዶሮ ዝይ ናት›› ከተሰኘ ኋላ-ቀር አመለካከት ለመላቀቅ፣ አንድ ኅይማኖት ብቻ ማወቅ በቂ እንዳልሆነ ያሰምርበታል—he who knows one religion knows none! ስለ ኅይማኖት ምንነት የተሻለ ግንዛቤ እንድኖረን ከተፈለገ፣ በተቻለ መጠን የራስን ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎችንም ኅይማኖት አጀማመርና ታሪክ (አመጣጥ) በጥልቀትና በስፋት ማጥናት ያስፈልጋል ማለት ነው።

ይሁን እንጅ፣ በዓለማችን ላይ አንድ ወጥ ኅይማኖት ብቻ እንድሰፍን ተግተው የሚሠሩ (ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው) ግለሰቦች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። እነኝህ ሰዎች የለሎችን የግል እምነትና ነፃነት የሚደፍሩ ሲሆን፣ ፍላጐታቸውም የራሳቸውን እምነት አሳድገው፣ የለሎችን ጨርሰው ለመደምሰስ ነው። ይህ ዘግናኝ እኩይ ድርጊት በዋናነት የሚመነጨው ከድንቁርና ነው። ስለሚንከተለው እምነት ምንነት በቂ ግንዛቤ ሳይኖረን፣ ‹የሃይማኖት እኩልነትን አንቀበልም› ብሎ ክላሽ ማንጣጣት ድንቁርና ካልሆነ በስተቀር ምንም ሊሆን አይችልም። ‹‹አድስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› ነው ነገሩ!

‹‹የለሎች ሃማኖት ጨርሰው መደምሰስ›› የሚል የድንጋይ ዘመን ፍልስፍና፣ በዘመኑ ዓለም ውስጥ (in contemporary world) ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። የሌላውን ሃይማኖት እየናቁ የራስን ማክበር በሳልነት አይደለም። ማንኛውም ሰው ነፃ-ፍቃዱን ተጠቅሞ የፈለገውን ሃይማኖት፤ እምነት እና አስተሳሰብ የመከተል ወይም የመያዝ ተፈጥሯዊ መብት አለው። ቅዱሳት መጽሐፍትም ይህንን እውነታ ያረጋግጣሉ፤ ‹‹የፈለገይመን የፈለገ ይካድ›› (አል-ከህፍ፤ 29) ‹‹በፊታችው ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና መርገምንእንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ›› (ኦሪት ዘዳ. 30፡ 19) በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 27 ማንም ሰው ያመነበትንና ህልናው የፈቀደውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመከተል ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው በግልጽ ያስቀምጣል። ስለዝህ፣ በዝ ረገድ ሕገ-ምንግስቱ የሚለንን ማክበር የግድ ይላል!

ስለዝህ፣ ‹‹የለሎች ሃማኖት ጨርሰው መደምሰስ›› የሚለው ሰይጣናዊ ፍልስፍና የሚያቀነቅኑ ሰዎች ይህንን መብት ከየት እንዳገኙ ለማወቅ እስካሁን ያደረኩት ጥረት አልተሳካልኝም። አቤ ጉበኛም እንድ ሲል ይጠይቃል፡- ‹‹እግዝአብሔር አንዱን ሐይማኖት ብቻ የሚወድ ቢሆን የሚወደውን የዓለም ሃይማኖት አድርጎ የቀሩትን አያጠፈቸውም? እሱ ካላጠፋቸውስ ማን ሊያጠፋቸው ይችላል? ከሱ የበለጠ እሱ የሚወደውን ነገር እናውቃለን? እንግድህ እግዝአብሔር በዕውቀቱ የሚያኖራቸውን ልዩ ልዩ ሃይማኖት የያዙ ሰዎች በልዩነት ማየትን እንተው።›› (አቤ ጉበኛ፤ አልወለድም፣ ገጽ. 81-82) ኬንያዊው ምሁር ፕ/ር ኪሁምቡ ታይሩ የአቤን ሐሳብ በፈረንጅኛ ስያጠናክር እንድህ በማለት ነበር፡-

‹‹The question that one has to ask is, what right has anybody got of telling you that the God of your people who has preserved you all these years (otherwise you would not be there), is a false God? To say that the God of a particular people is untrue is to declare that those people are themselves not quite people. This statement is fully illustrated by the examples in history where some nations were brutally exterminated without raising much trouble in the conscience of their exterminators because the former were ‘worshippers of false Gods.’” (Kihumbu Thairu, African Civilization 1975, pp. 67-68)

ነባራዊ እውነት አንድ ብቻ መሆኑን ፈጽሞ መካድ ባንችልም፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ በጊዜና በቦታ የተወሰነ በመሆኑ፣ እውነታን የሚረዳበትና የሚያብራራበት መንገድ (ዘዴ) የተለያየ ሊሆን ይችላል። ሃይማኖት እስከገባኝ ድረስ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ የሚሆነው በደመ-ነፍስ ተመርቶ ሳይሆን፣ ‹‹በእኔ እምነት ውስጥ በትክክል የእውነት ሙላት አለ፤ በፍጹም እኔን ሊያድነኝ የሚችለው እምነት ይኸኛውነው፣ ሃይማኖቴን የሚከተለው ከልብ በመነጨ ፍቅርና ደስታ እንጅ፣ ማንም ሰው ስላስገደደኝ አይደለም› ብሎ ከልብ ሰላመነበት ይመስለኛል። ይህ የሚያሳየው አንድ ሰው የቤተ-እምነቱን ቀኖና በሚገባ ስለተከተለ ብቻ ጽንፈኛ ተብሎ መፈረጅ የለበትም። ምክንያቱም፣ ጽንፈኝነት የሌላውን እምነትና አስተምሮ ማጥላላት እንጅ፣ የራስን ሃይማኖት ማክበርና ቀኖናውን በጽኑነትና በታማኝነት መከተል ጋራ የተያያዘ አይደለምና።

ስለዝህ፣ አንድ ሃማኖት የተከበረና የበላይ ሌላው የተናቀና የበታች አድርጎ ማቅረብ በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። በሃይማኖት ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት ከተፈለገ፣ ሃይማኖታዊ ልዩነቶቻችን ላይ ሳይሆን፣ የጋራ ሃይማኖታዊ እሰቶቻችን (ፍቅር፤ ሰላም፤ደስታ፣ ፍትሕ፣ ቅንነት፣ መልካም አሳቢነት፣ መከባበር…ወዘተ) ላይ ማተኮር የግድ ይላል። ‹‹ፍቅር መግዛት ከፈለግህ፣ ፍቅር ራሱ መክፈል ያለብህ ዋጋ ነው›› እንደሚባለው የእኛ እምነት ወይም አመለካከት እንዳይነካብን ከፈለግን፣ የሌላውን ሃይማኖት ፈጽሞ ማጥላላትና መናቅ የለብንም። በተለይ፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለፈውን ታሪክ እየነካኩ፣ የሌላውን ሃይማኖት ወይም እምነት ማጥላላት አደጋ አለው። ይህ ማለት ግን ትናንትና በሃይማኖት ምክንያት የተፈጸሙትን ስህተቶች አደበስብሰን ማለፍ አለብን ማለት አይደለም። ጥያቄው መሆን ያለበት ‹‹ከትናንትናው ታሪክ ምን እንማራለን?›› ነው! ኢሰባዊነት የተንጸባረቀባቸው አስከፍ ግጭቶች ዳግም እነዳይከሰት ከፈለግን፣ እያንዳንዳችን ካለፈው ታሪክ በመማር ለብዝሃ ኅይማኖት እውቅና መስጠት ይኖርብናል። ቆንጨራ ያላነሳ ሃይማኖት አልነበረምና፣ የታሪክ ሂሳብ እንወራረድ የሚል ግልብ አስተሳሰብየትም አያደርሰንም! አሜን!

ምንጭ፡- ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ፣ የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ፣ ገጽ. 74-75

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here